ቋሚ ኮሚቴው በመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አደረገ

ታኅሣሥ 11/2015 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ ሊያዳብሩ በሚችሉ ሀሳቦች ዙሪያ ውይይት አደረገ፡፡

ኮሚቴው ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከቀድሞው ሰራዊት ማህበር እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች ጋር ነው ውይይት ያደረገው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በመድረኩ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር እና ለማሻሻል የሚያስችሉ ሀሳቦች መገኘቱን ገልጸው ታኅሣሥ 14/2015 ዓ.ም ተጨማሪ ግብዓት ለመሰብሰብ የሕዝብ መድረክ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

በውይይቱ ወቅት ብርጋዴል ጀኔራል ይታያል ገላው ሰራዊቱ የቀድሞው እና የአሁኑ እየተባለ በሁለት ጎራ መከፋፈሉ መስተካካል እንደሚገባ አስረድተው ሁሉም መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ሉዓላዊነት ዘብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በደርግ ዘመን ወደ መከላከያ ሰራዊት የሚቀላቀለው ወታደር በግዳጅ እንደነበረ አስታውሰው አሁን ግን አምኖበት እና በፍቃደኝነት የሚቀላቀልበትን መንገድ በዝርዝር ማስረዳት አለብን ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured