ቋሚ ኮሚቴው በአፋር ክልል በአሸባሪው እየተፈናቀሉ ለሚገኙ ዜጎች አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል አለ

የካቲት 02/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ትሕነግ ቡድን ዳግም ወረራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአፋር ክልል ነዋሪዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጹ።

በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን ሰሞኑን በአፋር ክልል የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ቡድኑ ለትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑት የአፋር ክልል 14 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአፍዴራ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጎጂዎችንና የአከባቢው አመራሮችን አነጋግሯል።

ተፈናቃዮቹ አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ባደረሰባቸው የከባድ መሳሪያ ድብደባ መኖሪያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የት እንዳሉ ያልታወቀ በርካታ ዜጎች ስለመኖራቸው ነው ተፈናቃዮች ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ያስረዱት።

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን ጨምሮ ከተለያዩ ለጋሾች ሲደርስ የነበረው ሰብኣዊ ድጋፍም በአሸባሪው ቡድን ቁጥጥር ስር መዋሉን ከአብአላ ወደ አፍዴራ የተፈናቀሉ ዜጎች ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋውረው በአሸባሪው ቡድን ከቀያቸው ተፈናቅለው መንገድ ላይ የወለዱ እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካሞች እንዲሁም በጥቃቱ ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትን ተመልክተዋል።

የአፋርን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በጦርነት መግጠም የማይደፍረው የትሕነግ ኃይል ሰላማዊ ዜጎች ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን የአከባቢው አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ባደረጉት ምልከታ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በአሸባሪው ቡድን የከባድ መሳሪያ ጥቃት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ቁስለኞችን ጎብኝተዋል።

ጉብኝቱን ተከትሎም አባላቱ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

መንግሥትና የተለያዩ ለጋሾች ለአፋር ክልል እያደረሱ ላለው ሰብኣዊ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የክልሉ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ የተከፈተባቸው አዲስ ጥቃት በከባድ መሳሪያ የታገዘ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ብቻውን ሊቋቋመው እንደማይችል ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ (ዶ/ር) በበኩላችው በክልሉ እየተፈናቀለ እና አየሞተ ለሚገኘው ሕዝብ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሩ እልባት ለመስጠት ይሰራል ማለታቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡