ቋሚ ኮሚቴው የሁለት ዳኞችን ስንብት በሚመለከት ከዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጋር ተወያየ


ታኅሣሥ 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሁለት ዳኞችን የስንብት ሁኔታ በሚመለከት ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ ከዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጋር ተወያየ።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔው ዳኞቹ እንዲሰናበቱ የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ ሲያቀርብ በመሠረታዊነት ምክንያቶችን እንዲያብራራ ጠይቀዋል።

ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብም የዳኞች ስነ ምግባር ደንብን መሠረት የሚያደርግ ስለመሆኑ ስብሳቢዋ በጥያቄ ማንሳታቸው ተገልጿል።

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔው ያስተላለፈውን የውሳኔ ሃሳብ አስመልክቶ የቅጣት ማቅለያዎቹ ስራ ላይ ያልዋሉባቸው አሰራሮች ስለመኖሩም ጠይቀዋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር ጉባዔው ውሳኔውን ሲያስተላልፍ የዳኞችን የስነ ምግባር ደንብ መሠረት አድርጎ መሆኑን አንስተው ለስንበት የሚያበቁና መሠረታዊ ናቸው ካሏቸው ውስጥ የተከራካሪን የመሰማት መብት መጣስ፣ ሕዝብ በፍርድ ቤት ያለውን አመኔታ የሚያሳጡ ውሳኔዎችን መወሰን የሚሉት ለአብነት ከጠቀሷቸው ውስጥ ናቸው።

በመሆኑም የተፈጸመው ድርጊት እና ቅጣት ማቅለያው የሚመጣጠኑ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ገልጸው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤው የቅጣት ማቅለያውን የተመለከተው ቢሆንም ግን የፍትህ ስርዓቱ የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን እንደ እነዚህ አይነት የውሳኔ ሀሳቦችን በጥንቃቄ መመልከት እና መወስን አስተማሪነቱ ከፍተኛ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ለፍትህ ስርዓቱ ውጤታማነት ዳኞች የሚቀርብላቸውን የዳኝነት ጥያቄ በሕግ ላይ ተመስረተው መወሰን እንዲችሉ ስህተት ያለበትን በማረም ጥሩ የሚሰሩት የሚበረታቱበትን አሰራር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስገንዝበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ዳኞች የስነ-ስርዓት ጥሰት ሲፈጸሙ ከሚጣለው የገንዘብ ቅጣት ጎን ለጎን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሊሰጣቸው እንደሚገባ አንስቶ መዝገቦች ለዓመታት በዳኞች እጅ የሚቆዩበትን የአሰራር ስርዓት በማስያዣ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በፍርድ ቤቶች ያሉትን የአሰራር ክፍተቶች ቋሚ ኮሚቴው በተረዳው ልክ ሊስተካከሉ እንደሚገባቸው አንስተው የተወሰኑት ውሳኔዎች ለመታረም በቂ ዕድል የሚፈጥሩ ስለመሆናቸው ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።