ቋሚ ኮሚቴው የሕዝብን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ

አማረች ባካሎ (ዶ/ር)

ጥቅምት 7/2015 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2015 በጀት ዓመት የሕዝብን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሕዝብን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከር እና ጉድለቶችን በማረም እንደሚሰራ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር) አመላክተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅዶቹን ለማሳካት ሰባት ግቦችን ያስቀመጠ ሲሆን ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር ላለው የስራ ግንኙነት ትኩረት በመስጠት፣ ክትትል እና ቁጥጥር በማጠናከርና የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ በማተኮር በሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ተግባራትን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በኢንዱስትሪ እና ማዕድን ዘርፍ ያሉ ስራዎችን በማከናወን ረገድ የከበሩ ማዕድናት ልማት እሴትን የሚጨምሩ ኢንተርፕራይዞችን ከመጨመር እና ከማደራጀት አኳያ እንዲሁም የማዕድናት እና የወርቅ ኮንትሮባንድን ለማስቆም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ፣ ከምርት እስከ ሽያጭ ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ ለመስራት የሚያስችል የክትትል እና የቁጥጥር ስራ እንደሚያከናውን በቋሚ ኮሚቴው የእቅድ ግቦች ውስጥ የተቀመጠ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡

ለውጭ ንግድ የሚሆኑ ማዕድናትን በብዛት፣ በጥራት እና በአይነት ለማምረት፤ በነዳጅ የተፈጥሮ ጋዝ እና የሌሎች ማዕድናት ምርት እና ምርመራ እንዲሁም በሃይል ምርት ፍቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች አፈጻጸማቸው በእጥፍ እንዲጨምር ለባለድርሻ አካላት የሚሰጠው ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት፡፡

በ2014 ከአስፈጻሚ ተቋማት የተገኙ ግብአቶችን መሰረት በማድረግ ከተቋማት ጋር የፊት ለፊት መድረክ በመፍጠር መጠናከር ያለባቸውን በማጠናከር ጉድለቶችን በማረም ሀገሪቱ የተጣለባትን ተስፋ እውን የሚያደርግ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!