ቋሚ ኮሚቴው የተጓተቱ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ አሳሰበ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እየተጓተቱ ያሉ የመስኖ ፕሮክቶችን ማጠናቀቅ እንዳሚገባ አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያሳሰበው፣ ሰሞኑን በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንዳር፣ ምዕራብ እና ደቡብ ጎንዳር ዞኖች ተንቀሳቅሶ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በተመለከተበት ወቅት ነው፡፡

ምልከታ የተደረገባቸው የመገጭ፣ ርብ እና ሰረባ የመስኖ ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡ ተስፋ የጣለባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች በመሆናቸው የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሮቹ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባው ቡድኑ አሳስቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈትያ የሱፍ በበኩላቸው የፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ በጀት መንግስት ከአለም ባንክ በብድር ያገኘውና በምክር ቤቱ የጸደቀ መሆኑን አስታውሰው፤ የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት በ2005 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳልተጣናቀቀና ሌሎቹም የመስኖ ፕሮጅክቶች ለረጅም ጊዜ በመዘግየታቸው የህበረተሰቡን ቅሬታ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አማካሪዎችና ኮንትርክተሮች እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተናብበው በመስራት ለፕሮጀክቶቹ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን እንዲሚወጡ እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በማቅረብና  አዲስ ቡድን በማቋቋም ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚደርግ ገልፀዋል፡፡

የአማር ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፋንታሁን ማንደፍሮ በበኩላቸው  የፕሮጀክቶቹ መጓትት መንግስት ለቃሉ ታማኝ እንዳይሆን ማድረጋቸውንና የህዝብን አመኔታ እያሳጣን በመሆኑ ለቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአንክሮ በመስራት ለችግሮቹ እልባት መስጠጥ ይጠበቅበታል ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች  ምክር  ቤት  ያገኘነው  መረጃ ያመለክታል፡፡