በሀረሪ በ38 ሚሊየን ብር የተገነቡ መንገዶች ተመረቁ

ሚያዝያ 29/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል በ38 ሚሊየን ብር የተከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተመረቁ።

በክልሉ የሸዋል ኢድ በዓልን በማስመልከት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተመረቁ  ሲሆን በ38 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ በተገኙበት ተመርቀዋል።

በእለቱ የተመረቁት ሦስት የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ እነኚህም ከጂብራኤሎ እስከ ሲግቻ እንዲሁም ከሙጢ እስከ ድሬጠያራ እና ከስቁል እስከ ገንደ ጋራ የመንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በተለይም የገጠሩን ማኅበረሰብ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም የኅብረተሰቡን መሰረታዊ ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ሥራዎች እውን የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ በበኩላቸው መንገዱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሕዝቡን በባለቤትነት እንዲንከባከበው ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ125 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 9 የተለያዩ የገጠር መንገድ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ መንገድ ልማትና  ትራንስፖርት ቢሮ የገጠር መንገድ ሥራዎች ዳይሬክተር ደጀኔ አበራ ናቸው።

በእለቱ የተመረቁት ሶስት ፕሮጀክቶች 15 ነጥብ 9  ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ተመላክቷል።

ተስፋዬ ሀይሉ (ከሀረር)