በሀረሪ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ814 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ814 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ በቀለ ተመስገን እንደገለጹት በክልሉ በ2014 የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 814 ሚሊየን 726 ሺሕ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 814 ሚሊየን 838 ሺሕ ብር ተሰብስቧል።

የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ239 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

ከተሰበሰበው ገቢ መካከልም 424 ነጥብ 7 ከቀጥታ ታክስ፣ 244 ነጥብ 2 ሚሊየን ቀጥታ ካልሆነ ታክስ፣ 52 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም 93 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለገቢው ማደግም በተለይም ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥራዎችን ለማጎልበት በመከናወናቸው እና በደረሰኝ አቆራረጥ ላይ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የክልሉ ገቢን ለማጎልበት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ 1 ቢሊየን 64 ሚሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ከቢሮው የተገኘ መረጃ አመላክቷል።