በሀረሪ ክልል ባሉ ት/ቤቶች 75 በመቶ የትምህርት ግብአት አልተሟላም

ሚያዝያ 9/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ባሉ ትምህርት ቤቶች 75 በመቶ የትምህርት ግብአት ሙሉ በሙሉ አለመሟላቱ ተገለፀ፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙኽታር ሳሊሕ የትምህርት ሴክተሩን አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በዚህም በክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች 75 በመቶ የትምህርት ግብአት ሙሉ በሙሉ ያልተሟሉላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የትምህርት ግብአት ሙሉ በሙሉ የተማሉበት ትምህርት ቤቶች 25 በመቶ ብቻ ናቸው ይህ ደግሞ ትምህርት ጥራቱ ላይ ተፅእኖ አለው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ጥናቱ ከ2008 – 2013 ባለው ጊዜ ከ5-8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ውጤት እየወረደ መሆኑን አሳይቷል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ለአብነትም በ2013 የ8ኛ ክፍል ከተፈተኑ ተማሪዎች 50 በመቶ ማግኘት የቻሉት 24 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በ2013 አመት 12ተኛ ክፍል ተፈታኞች መካከል 20 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸውም ተገልጿል፡፡

የሀረሪ ክልል በብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሀመድ በትምህርት ዘርፍ የተካሄደው ጥናት ላይ የታየው ውጤት ቀደም ሲል በትምህርት ሴክተሩ ላይ የነበሩ አመራሮች ሥራ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የወረዳውን የተማሪዎች ውጤት ከፍ ለማድረግ የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በትምህርት ሴክተሩ ውስጥ የሚታዩ በጀትን በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር በመመሪያው መሠረት ቅጥር አለመፈፀም እኛ ሌሎችንም ችግሮች የወረዳዎች ፖለቲካ አመራሮች አጣርተው ለትምህርት ቢሮ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፡

በሚቀጥሉ 3 ወራት ችግሩን ለመፍታት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ዘግቧል፡፡