በሀረሪ ክልል ነገ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ለኅብረተሰቡ እንደሚከፋፈል ተገለጸ

መጋቢት 5/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ከነገ ጀምሮ 54 ሺሕ ሊትር ዘይትና 2 ሺሕ ኩንታል የስንዴ ዱቄት ለኅብረተሰቡ እንደሚከፋፈል የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ቡሽራ አሊዪ እንደገለፁት በክልሉ ህገወጦችን ከመቆጣጠር ባለፈ በመንግሥት ድጎማ የሚቀርቡ የምግብ ሸቀጦችን በአግባቡ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከነገ ጀምሮም ገበያን ለማረጋጋት በመንግሥት ድጎማ የቀረቡ 54 ሺሕ ሊትር የምግብ ዘይት እና 2 ሺሕ ኩንታል የስንዴ ዱቄት በክልሉ በከተማና በገጠር በሚገኙ ዩኒየኖች አማካኝነት ለኅብረተሰቡ እንደሚከፋፈል ገልፀዋል፡፡

በዚህም ባለ20 ሊትር ዘይት 1848 ብር፣ 5 ሊትር በ462 ብር እንዲሁም አንድ ሊትሩን በ93 ብር ከ50 ሳንቲም እንዲሁም አንድ ኪሎ ስንዴ ዱቄት በ39 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሚከፋፈል ጠቁመዋል፡፡

የዋጋ ንረት እንዲባባስ በሚያደርጉ ህገ ወጥ ነጋዴዎች የመቆጣጠር እና ወደ ህጋዊነት እንዲመጡ የማድረግ ሥራም ትኩረት እንደተሰጠውም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘን 150 ሺሕ ሊትር የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር ውሎ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መከፋፈሉን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡