በሀረሪ ክልል የመማር ማስተማር ስራ በዛሬው እለት ተጀምሯል

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የመማር ማስተማር ስራ በዛሬው እለት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ሀላፊ ሙክታር ሳሊህ እንደገለፁት በ2015 የትምህርት ዘመን ባለፈው አመት የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን በማጠናከርና የታዩ ክፍተቶችን በማረም ውጤታማ የመማር ማስተማር ስራ ማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

በክልሉ በ2015 የትምህርት ዘመን ለትምህርት የደረሰ ሁሉም ታዳጊ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገባ ለማስቻልም ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ትምህርት ቤቶችም ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ የማድረግ ስራ ስለመሰራቱ አንስተዋል።

በአመቱ በክልሉ አጠቃላይ መመዝገብ ከሚገባቸው 93 ሺሕ ተማሪዎች መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

በ2015 የትምህርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ የመንግስትና የግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የሙከራ ትግበራ ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል።

የ2015 የትምህርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ በዛሬው እለት መጀመሩን ጠቁመው የትምህርት ዘመኑ ውጤታማ እንዲሆን  የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሐረር ቅርንጫፍ)