በሀረሪ ክልል የሚካሄደው ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 25/2013 (ዋልታ) – በሀረሪ ክልል የሚካሄደው መቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ የሚገኙ የመንግስትና የፀጥታ አካላት አመራሮች በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ አቶ ናስር ዩያ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወረዳዎች ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሰላምን ከማስጠበቅ አንፃር በትኩረት መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከሪያ በክልሉ በአሁኑ ወቅት እየታየ የሚገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጠናር የክልሉ ፖሊስ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በተለይም በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እና በሀላፊነት መስራት አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡