በሀረሪ ክልል የኢድ በዓላትን በተሳካ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ሚያዝያ 4/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል “ከኢድ እስከ ኢድ” እና የሸዋል ኢድ በዓላትን በተሳካ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በክልሉ ከኢድ እስከ ኢድ እና የሸዋል ኢድ በዓላት አከባበርና ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች አስፈላጊን መስተንግዶ እንዲያገኙ ለማስቻል የተቋቋመው ዓብይ ኮሜቴ በክልሉ ከበዓላቱ ጋር ተያይዞ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ገምግሟል።
ከኢድ እስከ ኢድ ዓብይ ኮሚቴ ባካሄደው ውይይትም በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት በሚመለከት ከኮሚቴው አባላትና የተቋማት አመራሮች ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን ኮሚቴውም በቀረበው ማብራሪያ መነሻ በማድረግ ተወያይቷል፡፡
ከከተማው ፅዳትና ውበት ጋር ተያይዞ፣ የፕሮጀክት አፈፃፀምን ከማጎልበት አንፃር፤ ሰላምና ፀጥታን ከማጠናከር በዋናነትም ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ኩነቶችን ከማዘጋጀት አንፃር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ላይ መምከራቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል።
ከኢድ እስከ ኢድ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ አብዶሽ እንደተናገሩት በክልሉ አጠቃላይ ከኢድ እስከ ኢድ እና ከሸዋል ኢድ በዓላት ጋር ተያይዞ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።