በሀረሪ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽ እና ጥራት እንዲጎለብት በትኩረት ይሰራል ተባለ

የካቲት 10/2015 (ዋልታ) በክልሉ ለአንድ ወር በተካሄደ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባላት ምዝገባና እድሳት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አባላቱ የተሟላና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ይገባል።

በክልሉ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የጤና ተቋማት በሰው ሃይል፣ በክህሎትና በእውቀት የተካኑ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመው አገልግሎት አሰጣጥን ማጎልበት ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአባላትን እርካታ ለመጨመር በጤና ተቋማት የሚታየውን የመድሃኒትና ሌሎች ግብዓቶች እጥረትን ለመቅረፍ እና የህክምና አገልግሎቱን ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው በክልሉ ለአንድ ወር በተካሄደው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባላት ምዝገባና እድሳት ንቅናቄ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

በንቅናቄውም 45 ሺህ 539 እማወራዎችና አባወራዎች የአባላት እድሳት ማድረጋቸውን እና 164 አዳዲስ እማወራዎችና አባወራዎች አባል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በመድረኩም ለአንድ ወር የተካሄደው ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫ)