በሀረር ከተማ “አካባቢያችንን ከቆሻሻ ሀገራችንን ከአሸባሪዎቹ እናፀዳለን” በሚል የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ

ኅዳር 12/2014 (ዋልታ) በሀረር ከተማ “አካባቢያችንን ከቆሻሻ ሀገራችንን ከአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ እናፀዳለን” በሚል መሪ ቃል የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ፡፡

በፅዳት ዘመቻው የክልሉ ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎችና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በሀረሪ ክልል ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ላይ የተገኙት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት አሁን ባለንበት ፈታኝ ወቅት ማለፍ የምንችለው በአንድነትና በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ነው፡፡

የኅልውና ዘመቻውን ከማሳካት ጎን ለጎን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በቁርጠርነት ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመው በእለቱ የተደረገው ፅዳትም ተነሳሽነት እንዲፈጠርና የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲጠናከርና የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አንፃርም የሀረር ከተማ ህዝብ በተደጋጋሚ የሚያነሳው ቅሬታ ከመቅረፍ አንፃር አመራሩ አርዓያ ሆኖ መንቀሳቀስና በቀጣይ ሀረርን ፅዱና ማራኪ ለቱሪስቶች ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም በቀንና በማታ በቁርጠኝነት እየጠበቀ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከውስጥና ከውጭ እየደረሱ ያሉ ጫናዎችን የምንመክተው በአንድነት በመንቀሳቀስ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም ህዝቡ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም አንድነቱን አንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡ በቀጣይም መሰል ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ኡስማኤል ዩሱፍ በበኩላቸው እንደተናገሩት የከተማው ማዘጋጃ ቤት በከተማው እየተስተዋለ የሚገኘውን የፅዳት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በእለቱም አካባቢያችንን ከቆሻሻ ሀገራችንን ከአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ እናፀዳለን በሚል መሪ ቃል በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የፅዳት ዘመቻ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

ከፅዳት ባሻገርም የመንገድ መብራትና ሌሎች ተግባራት በቁርጠኝነት እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ህዝቡ ከተማውን ፅዱና ለነዋሪው ምቹ ከተማ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ሚናውን እንዲያጎለብት መጠየቃቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡