መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ሪፎርሙ 6 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስር ዓመቱ የሀገር በቀል የሪፎርም እቅድ የሶስት ዓመታት አፈጻጸም ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጻ አድርገዋል፡፡
የሶስት ዓመቱ የሪፎርም አጀንዳዎች ሀገሪቱ ያለባትን ብድር መቀነስ፣ ተጀምረው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን መጨረስ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ማሳደግና ማሻሻል ላይ ያለመ ነበር ብለዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጎርፍ አደጋዎች መፈጠር፣ የአንበጣ መከሰት እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች የሪፎርም እቅዱ ፈተናዎች ነበሩ ነው ያሉት፡፡
ሀገሪቱ እነዚህን ቸግሮች ተቋቁማ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋን (GDP) ከ100 ቢሊየን ብር በላይ በማድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዘግተው የነበሩና ለውጭ ገበያ ምርት ለሚያቀርቡ ድርጅቶች የሚፈለገውን ድጋፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን በ21 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተያዘው ዓመት በስምንት ወራት 191 ቢሊየን ብር ከውጭ ገበያ መሰብሰብ መቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በግብርና ምርት፣ በመንገድ ግንባታ፣ በጤና እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እድገት እየተመዘገበ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚታይ ግን በቂ ያልሆነ እድገት መመዝገቡንም አስረድተዋል፡፡
(በብርሃኑ አበራ)