በሃገር ክህደት እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በነበሩ አመራሮች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ መንግስት እና ህዝብ የጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው መቀመጫቸውን ትግራይ ክልል በማድረግ የህዋሓት ፀረ-ሠላም እና ፀረ-ህዝብ ከሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ተልዕኮ መቀበላቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በጽንፈኝነት አስተሳሰብ በመነሣት በሀይል ወደ ስልጣን የመምጣት ፍላጎትን ካነገቡ ፀረ-ሠላም ሀይሎች ተልዕኮ በመቀበል በሀገር ውስጥ ሌሎችን በማደራጀት ሀገር የመበተን፣ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር እና ህገ-መንግስታዊ ሥርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ውስጥ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ በመሳተፍ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው በማድረግ በሃገር ክህደት እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ በተለያዩ የአመራር ደረጃ ላይ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል ነው ያለው፡፡
የመያያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው ተጠርጣሪዎች
- ኮማንደር ሰለሞን አብርሃ ብስራት
- ኮማንደር ሀይለማርያም ብርሃኔ ገብረማርያም
- ምክትል ኢንስፔክተር ክብሮም ገብሩ ገብረእግዚአብሄር
- ምክትል ኢንስፔክተር አረጋዊ ገብረሂወት አስፋው
- ረዳት ኢንስፔክተር ገዛኢ ገብረሂወት ገብረስላሴ
- ረዳት ኢንስፔክተር ተስፋ ኪሮስ ግደይ
- ረዳት ኢንስፔክተር አርአያ ገብረአናንያ ኪዳኑ
- ረዳት ኢንስፔክተር ሰለሞን ወላይ ወልደአብዝጊ
- ዋና ሳጅን ሀይላይ ወልዱ ገብረማርያም ናቸው።
በመሆኑም መላው ህዝብ በተለይም ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ፣ እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ ሰራዊትና የደህንነት ተቋማት እነዚህን የጁንታው የህዋሓት የጥፋት ቡድን ተፈላጊዎች አባላትን አድኖ ለህግ ለማቅረብ እየተደረገ ባለው ተግባር በያሉበት የድርሻቸውን እንዲወጡ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በቀጣይም የጁንታው ርዝራዥ ቡድን ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በመግለጽ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለህብረተሰቡ ይፋ እንደሚያደርግ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡