በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ170 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ተያዘ

ሐምሌ 20/2013(ዋልታ) – በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ170 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በህገ ወጥ መንገድ የአሜሪካ ዶላር ሲያዘዋውር የነበረው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-57949 ኢት/ተሳቢ 17713 ኢት የሆነ ከባድ ተሽከርካሪ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቅንጅት በተደረገበት ክትትል በቁጥጥር ስር የዋለው ሃምሌ 7 ቀን 2013 ዓ/ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ቱሉ ዲምቱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው፥ ተሽከርካሪው ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ እየተጓዘ የነበረ ሲሆን፥ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በተደረገበት ፍተሻ ከጋቢናው መቀመጫ ወንበር ጀርባ በሚገኝ ሳጥን ውስጥ በላስቲክ ተጠቅልሎ የተደበቀ 170 ሺህ 700 የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ዉሏል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ አንድ ተጠርጣሪ ተይዞ ምርመራው በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ  የአዲስ አበባ ፖሊስ መጥቀሱን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ህገ- ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር የሃገርን ሰላም እና የተረጋጋ ኢኮኖሚን በማናጋት በህዝብ ኑሮ ላይ የሚፈጥረው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ መረጃ እና ጥቆማ በመስጠት ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡