በህገ ወጥ መንገድ ነዳጅ ለማጓጓዝ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መጋቢት 1/2014 (ዋልታ) በህገ ወጥ መንገድ 39 በርሜል ነዳጅ ጭነው ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ከተማ ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦችና ሁለት የማደያው ሰራተኞች ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ግለሰቦቹ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ ማርያም አካባቢ ከሚገኝ ኖክ ፈጣን ነዳጅ ማደያ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 A 10734 አ/አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ ነዳጅ በመቅዳት ሲያጓጉዙ መያዛቸውን ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ከኅብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በተወሰደ እርምጃ 50 በርሜል ተዘጋጅቶ ሰላሳ ዘጠኝ በርሜል ናፍጣ ተቀድቶ የተያዘ ሲሆን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የተያዘው ነዳጅ 7 ሺሕ 800 ሊትር መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ግለሰቦቹ መመሪያ ቁጥር 12/2011 አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 16 ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ምንም አይነት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው ነዳጁን ለማጓጓዝ ሲሞክሩ ተይዘዋል።

ህገወጦቹ በኅብረተሰቡ ጥቆማ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆ መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙ ጥቆማ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ከአገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የሚንቀሳቀሱ አካላት እና በህጋዊ የንግድ ፍቃድ ሽፋን ህገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከህገወጥ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንዲሚገባ ፖሊስ ማሳሰቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW