በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ሲቀበሉ የተገኙ ደንብ አስከባሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር የግንባታ ቤትን ምክንያት በማድረግ ያለ አግባብ ገንዘብ ሲቀበሉ የተገኙ ሁለት የደንብ ቁጥጥር ባለሙያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ጌታሁን አበራ ባለሙያወቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው ግንባታ የሚያከናውኑ ግለሰብን ፈቃድ የሌላቸው በማስመሰልና እናስፈርሳለን በማለት ገንዘብ እንዲከፍሉ በማስገደድ ግለሰቡ ለፀጥታ አካላት በሰጡት ጥቆማ ብር ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ህገ-ወጦችን ለመከላከል አስተዳደሩ በሚሰራው ሥራዎች በባለቤትነት በመያዝ እና የእጅ መንሻን በመቃወም ለክፍለ ከተማው ሰላም መስፈን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ህገ-ወጥ ተግባራትን በመጠቆም እንዲተባበር ጥሪ ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።