በሊጉ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባሕር ዳር ከተማ ድል ቀናቸው

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ባሕር ዳር ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምረዋል።

ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተጀምሯል።

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አምበሉ ጌታነህ ከበደ በ50ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ድንቅ የቅጣት ምት ጎል አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በሌላኛው ጨዋታ ባሕር ዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በድጋሚ የተመለሰውን ኢትዮ-ኤሌትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ዱሬሳ ሹቢሳና ተስፋዬ ታምራት ለጣና ሞገድ ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል።

ስንታየሁ ዋለጩ ለኢትዮ-ኤሌትሪክ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርኃ ግብር በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቀጥሎ ሲውል በነገው ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ኢትዮጵያ መድን ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይጫወታል።

እንዲሁም ከቀኑ 10 ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ ከቀኑ 7 ሰዓት ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና፤ ሐዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎውን ከሚያደርገው ለገጣፎ ለገዳዲ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ እንደሚጫወቱ የኢዜአ መረጃ አመልክቷል።

የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርኃ ግብሮች በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም (ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሳምንት)፣ በድሬዳዋ ስታዲየም (ከስድስተኛ እስከ 10ኛ ሳምንት) እና በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ሜዳ (ከ11ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት) ይከናወናሉም ተብሏል።