በላስ ቬጋስ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ መንግስት የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – በላስ ቬጋስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ መንግስት የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የህወሃት ቡድን በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም በሀገራቸው የፈፀመውን የሰላም ማደፍረስ እና የክህደት ወንጀል በማውገዝ እና በሕወሃት ስርዓት ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የዳያስፖራ ቡድኖች አባላት ግፊት እና በስርቆት ገንዘብ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ በአንዳንድ የአሜሪካ የህግ አውጪ እና የህግ አስፈፃሚ አካላት የሚደረገውን ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫናን በመቃወም ነው ሰልፉን ያካሄዱት።

በሰልፉ  ላይ በርካታ የላስቬጋስ ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተሳተፉ ሲሆን፣ ሰልፉን ያስተባበሩት በላስ ቬጋስ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ እና የላስ ቬጋስ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ንዑስ ቡድን አባላት ናቸው ተብሏል።

የዳያስፖራ አባላቱ ለሀገራቸው እና ለመንግስት ያላቸውን ድጋፍ የገለፁ ሲሆን፣ በዲፕሎማሲው ረገድ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ኢ-ፍትሃዊ ጫና በተደራጀ መንገድ ለመቋቋም ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ለመታገል መወሰናቸውን አረጋግጠዋል።

ሰልፈኞቹ፣  የጁንታው ቡድን እና ተባባሪዎቹ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀሎች በማውገዝ፣ አሜሪካን ጨምሮ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በጥንቃቄ በመመርመር ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጥ ጥሪ የሚያቀርቡ እና ሌሎችም ወቅታዊ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ሰልፈኞቹ ጥያቄያቸውን በኔቫዳ ግዛት ተመራጭ ለሆኑ ሁለት ሴናተሮች እና አራት የኮንግሬስ አባላት በፅሁፍ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።