መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – ሀይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘው ላፍቶ አትክልት ተራ በሁለት ግለሰቦች መካካል በተፈጠረ ፀብ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡
ዛሬ ከጠዋቱ በግምት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በሁለት የጉልበት ሰራተኞች መካከል በስራ አለመግባባት ምክንያት በተፈጠረ ፀብ የአንደኛው ሕይወት ማለፉን እና ገዳዩ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የተወሰኑ ግለሰቦች የግድያ ወንጀል በፈፀመው ተጠርጣሪ ላይ ጉዳት ለማድረስ በፈጠሩት ፀብ ምክንያት በፖሊስ አባላትና በአካባቢ ጥበቃ ስራ በተሰማሩ አጋዥ ሀይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ግርግሩን ለማብረድ ፖሊስ ባደረገው ጥረት አካባቢው ተረጋግቶ መደበኛ ስራ መጀመሩን እና ግርግር በማስነሳት ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሁለት ብሔሮች መካከል ፀብ እንደተነሳ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ ሀሰተኛ እንደሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡