በሐዋሳ ከተማ በ20 ሚሊየን ብር ወጪ ሁለገብ የስፖርት ማዕከል ሊገነባ ነው

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – በሐዋሳ ከተማ በ20 ሚሊየን ብር ወጪ ሁለገብ የስፖርት ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የከተማ መስተዳድሩ አስታወቀ።

የከተማዋ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካዊሶ የከተማዋን ወጣቶች በስፖርት ሜዳ ውሎ በየጊዜው በውጤት የታጀበ ቢሆንም፤ ከፍተኛ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት መኖራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የተነሳ ለከተማዋ፣ ለክልሉም ሆነ ለሀገር ከዘርፉ መገኘት ያለበት ጥቅም እንዳልተገኘ የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፣ በዚህም ኪሳራ ውስጥ እንደገባን ይሰማናል ብለዋል፡፡ በተለይ ስፖርት ፍቅር፣ አንድነት እና ሰላም የሚሰበክበት ትልቁ መሳሪያ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ አበክሮ አለመስራት አግባብ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ከችግሩ የተነሳ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ሊያስጠሩ የሚችሉ ብርቅዬ ወጣቶች አቅም ተደብቋል ያሉት አቶ ጥላሁን፣ እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ማዕከሉን መገንባት አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ስፖርት እና ስፖርተኞች በዓለም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን እያንቀሳቀሱ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ኢትዮጵያ በዚህ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ መሪ ተዋናይ አለመሆኗ አሳዛኝ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በአገር ደረጃ ለስፖርት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነና መሰል የስፖርት ማዕከላትንና ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባት ያላቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንድምታ ከፍ ያለ እንደሆነም አመልክተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።