ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በያዛቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አበርገሌ ወረዳ 12 ቀበሌዎች ውስጥ በተቀሰቀሰ ወረርሽኝ ህፃናት ለሞት እየተዳረጉ በመሆኑ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ድንበር የለሽ የህክምና ተቋማት ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጤና መምሪያ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በዞኑ በሚገኘው አበርገሌ ወረዳ አሸባሪው ሕወሓት በያዘባቸው 12 ቀበሌዎች ዓይነቱ በውል ያልታወቀ አዲስ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡
በተከሰተው ወረርሽኝም እስካሁን የዘጠኝ ህጻናት ህይወት ማለፉ ነው የተገለጸው፡፡
አሁን ላይ አካባቢዎቹ በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በቁጥጥር ስር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ለዜጎች አስፈላጊውን የጤና ባለሙያ እገዛ መስጠት አለመቻሉንም ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡
ስለሆነም መንግሥት በአካባቢው የሚገኙ ዜጎችን ከወረርሽኙ ለመታደግ አስቸኳይ የምግብና የመድሐኒት እርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ በፍጥነት እንዲመቻች ከዓለም ዐቀፍ ድንበር የለሽ የህክምና ተቋማት ጋር በመነጋገር አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን ሲል መምሪያው ጠይቋል፡፡
የአብርገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አለሙ ክፍሌ ወረርሽኙ በዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን የተከሰተ መሆኑን ጠቁመው ከህጻናት ባሻገር አዛውንቶችም እየተያዙ ነው፡፡
አበርገሌ ወረዳ እስካሁን ከአንድ ዓመት ስድስት ወር ገደማ በጠላት ስር መሆኗን የገለጹት አስተዳዳሪው እስካሁን በአካባቢው በረሃብ፣ በእርዛትና በበሽታ ምክንያትከ 120 ሰው በላይ ዜጎች ህይወት ማለፉን ጠቁመዋል፡፡