ሚያዝያ 29/2014 (ዋልታ) በሕገ-ወጥ መንገድ የተደራጁ የጫኝና አውራጅ ማኅበራት በማኅበረሰቡ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ተገለፀ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጫኝና አውራጅ ምክንያት በማኅበረሰቡ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎች ዙርያ ውይይት ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማኅበረሰብ ዐቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ፋንታው በከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከመጋዘን ዕቃ በሚወርድበት ወቅት ተደራጅተናል እኛ ነን የምናወርደው በማለት ችግር መፍጠር፣ ባለሃብቶች በራሳቸው ለማውረድ ሲሞክሩ መከልከል፣ ለማውረድ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ እንዲሁም ገንዘብ አስገድዶ መቀበል እንደ ችግር እየተስተዋሉ ነው ብለዋል፡፡
ሕጋዊ ሆነው የተደራጁ የጫኝና አውራጅ ማኅበረሰብ አባላት መብትና ግዴታቸውን አለማወቅ፣ አደራጅ አካላትም ከማደራጀት ባለፈ ሕዝቡን በትክክል እያገለገሉ ስለመሆኑ ክትትል አለማድረግ፣ ማኅበረሰቡም ችግሮች ሲፈጠሩ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ አለመስጠት ለችግሮቹ መበራከት ምክንያት መሆናቸው ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍስሃ ጋረደው በበኩላቸዉ ሥራቸውን አክብረው የሚሰሩ አባላትን በማመስገን ማኅበራትን በደረጃቸውና በሥራቸው በመገምገም በቅርበት ጤናማና ጤናማ የሆኑትን ለመለየት እንሰራለን ብለዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ በሕገ-ወጥ መንገድ ተደራጅተው ማኅበረሰቡን የሚያንገላቱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እና በየጊዜው የሚሰሩ ሥራዎች የደረሱበትን መገምገም መፍትሔ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በአሳንቲ ሃሰን