በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ዝውውር የተሰማሩ ግለሰቦች ተያዙ

የካቲት 28/2014 (ዋልታ) በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ዝውውር የተሰማሩ ግለሰቦች ከሚያዘዋውሩት ህገወጥ ንብረት ጋር በቁጥጥር መዋላቸው ተገለጸ።

ተጠርጣሪዎቹ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ክትትልና ጥቆማ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መነሻቸውን አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ያደረጉ ሁለት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰቦች ሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ ፖሊስ 0433 አ.ማ በሆነ የአማራ ልዩ ኃይል ፓትሮል ላይ 14 ሺሕ 669 የቱርክ ሰራሽ እና የማካሮቭ ሽጉጥ ጥይት በመጫን መዳረሻቸውን ባሕር ዳር ከተማ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ዘንዘልማ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

በተመሳሳይ መነሻውን አማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ ያደረገ አንድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰቦች 14 ሺሕ 600 የቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ጥይት በመጫን መዳረሻውን ደሴ ከተማ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በተደረገ ክትትል ክምር ድንጋይ ከተማ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

መነሻውን በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ ያደረገ አንድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ ሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3 A 35881 በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ ላይ 1 የብሬንና 1 የብሬን ጥይት መያዣ ዝናር፣ 978 የክላሽ ጥይት እና 3 ሚሊዮን ብር የተፃፈበት ደረቅ ቼክ በማዘጋጀት መዳረሻውን ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በማድረግ ለኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ለማቀበል በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በተደረገ ክትትል አዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከነጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር ውሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቡራዩ አካባቢ ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በተደረገ ፍተሻ 5 የተለያየ መጠን ያለው የብሬን ጥይት መያዝ የሚችል ዝናር ተገኝቷል።

ከህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ መነሻውን አዲስ አበባ ከተማ ያደረገ አንድ ህገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪ ግለሰብ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ 87 ሺሕ 311 የአሜሪካን ዶላር በመጫን መዳረሻውን ቶጎ ወጫሌ ለማድረግ በመጓዝ ላይ እያለ በተደረገ ክትትል በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን ቀርሳ ከተማ ኬላ ላይ ከነ ገንዘቡ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል፡፡