በመተከል መስከረም ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ነው

ነሀሴ 22/2013 (ዋልታ) – በመጪው መስከረም ወር በመተከል ዞን ለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በዞኑ በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ነው የገለፁት።

በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩ ከ58 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወደየወረዳቸው ማሰባሰብ መቻሉ ምርጫውን በአካባቢያቸው እንዲመርጡ የሚረዳ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡
የፀጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ ለማድረግም በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተመለመሉ ሚሊሻና ምልሶችን አሰልጥኖ በማስታጠቅ የአካባቢያቸውን ፀጥታ እንዲያስከብሩ የማድረጉ ስራ በስኬት እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት።
ግቡን ለማሳካት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ እና የሲዳማ ልዩ ሀይሎች ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሃያ አራት ሰአት ግዳጃቸውን በጀግንነት እየፈፀሙ ይገኛሉ ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።