የካቲት 03/2013 (ዋልታ) – የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በመተከል ዞን ለደረሰው ግድያና ውድመት ይቅርታ ጠየቀ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጉባኤ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
ጉባኤው በአሶሳ ከተማ በክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካና የሠላም ሁኔታ ላይ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
በዚህም ፓርቲው በክልሉ መተከል ዞን በደረሰው አሳዛኝና ዘግናኝ ማንነት ተኮር ግድያና ውድመት ይቅርታ ጠይቋል፡፡
የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ‘ብልፅግና አሀዳዊ ነው’ በሚል የሀሰት ትርክት ከሁለት ቦታ በመርገጥ ህዝብን ሲበድሉ የነበሩ አመራሮች መኖራቸውም ተገምግሟል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ በቀጣይ የህግ የበላይነትን በማስከበር በወንጀል የተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
የፓርቲውን እሴትና መርህን በማክበር የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም በአቋም መግለጫው ተመላክቷል።