ነሃሴ 06/2013 (ዋልታ) – በመተከል ዞን የህወሓትን ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ወጣቱ መዘጋጀት እንዳለበት ኮማንድ ፖስቱ አሳሰበ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበትን ቀጠና ለማተራመስ በተነሳው ሃይል ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ወጣቱ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ህግን ማስከበር እንዳለበት የ22ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሰይፈ ኢንጌ አሳስበዋል።
በመተከል ዞን የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዛሬ ጀምሮ ያላቸውን የጦር መሳሪያ በማስመዝገብ በቀጠናው እየተንቀሳቀሰ ያለውን የሽፍታ ቡድን ማስወገድ አለበት በማለት ኮማንድ ፖስቱ ጥሪ አቅርቧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት የጸጥታ ዘርፍ አማካሪ አቶ አብደላ ሸኸዲን በበኩላቸው የሽፍታው ቡድን ሰላማዊ ዜጎችን በመንገድ ላይ በማስቆም ህይወት እየቀጠፈ በመሆኑ ይሄን ለማስወገድ በቁርጠኝነት በመነሳት እና በመመከት የቀጠናውን ሰላም ማስመለስ ይገባል ብለዋል።
በመተከል ዞን የአሸባሪ ቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ሽፍታ ለማስወገድ የሁሉም ሚና አስፈላጊ መሆኑን አቶ አብደላ ተናግረዋል ሲል የመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።