በመተከል ዞን የጠላትን ኃይል በመደምሰስ የጦር መሳሪያዎች ተማረኩ

ነሐሴ 16/2014 (ዋልታ) በመተከል ዞን በዳንጉር ወረዳ በተካሄደው ኦፕሬሽን የጠላትን ኃይል በመደምሰስ የጦር መሳሪያዎች ተማረኩ፡፡

የዞኑ ሰላም ግንባታና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም ዋቅጅራ እንደገለጹት ትናንት በዳንጉር ወረዳ በተካሄደው አፕሬሽን 4 የጠላት ኃይል አባላት ሲደመሰሱ ሞርተር፣ ዲሽቃ ብሬን እና ክላሽና ሌሎች መሳሪዎች ተማርከዋል፡፡

የቀጠናውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በዞኑ የሚመራ ኦፕሬሽን በማደራጀት የጠላት ኃይል እየተዳከመ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የዳንጉር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ሃብታሙ ባማኑ በበኩላቸው እየተካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የወረዳው የሚሊሻ አባላት የሚሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣትና የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን ዝግጁ መሆናቸውን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡