ሚያዚያ 04/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ያለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ገለጹ።
የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች በዞኑ በመገኘት በአካባቢው ያለውን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በዞኑ ከተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሃይል አመራሮች እንዲሁም ከዞኑ የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ከፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በየደረጃው የተካሄደውን ውይይት በማስመልከት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአካባቢው የታጠቁ ሽፍቶች በፈፀሙት ጥቃት ዜጎች የሞቱበት፣ በርካቶች የተጎዱበት እንዲሁም ንብረቶች የወደሙበት መሆኑን አንስተዋል።
ሆኖም በዞኑ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ስራ ከጀመረ ወዲህ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እየታየ መምጣቱን በየደረጃው ከነበረው ውይይት መረዳታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው “ተዋልዶና ተጋምዶ” የሚኖረውን ህዝብ በማጋጨት ለማለያየት ፀረ ሰላም ሃይሎች ብዙ ጥረት ማድረጋቸውንም አፈ ጉባኤዎቹ ገልጸዋል።
በየደረጃው በነበረው ውይይት መረዳት የተቻለውም በህዝብ ውስጥ ምንም አይነት ችግር እንደሌለና አብሮነቱን፣ ልማቱንና ሰላሙን በጋራ የማምጣት ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው በቀጣይ ሞትና መፈናቀል እንዳይከሰትና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም የየድርሻቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተው መንግስትም ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ስራውን እንዲያጠናክር የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
በመንግስት በኩል በዞኑ ያለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል።
“በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በየደረጃው ያለው የአመራር ብቃት እየተፈተሸ ማስተካከያ በማድረግ ለዞኑ ብሎም አጠቃላይ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል አፈ ጉባኤዎቹ።
ለዚህም የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ በየደረጃው ያለ አመራርና አጠቃላይ ማህበረሰቡ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ለኢዜአ አመልክተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ሂደት ኮማንድ ፖስቱ በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።