የካቲት 18 /2013 (ዋልታ) – በመንገድ ደህንነት ችግር የሚከሰተው የሞት መጠን ባለፉት ስድስት ወራት 15 በመቶ መቀነሱን ብሔራዊ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።
የትራንስፖርት ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በጉባዔው መክፈቻ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ አስከፊውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የትራፊክ አደጋ ምጣኔን መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከኮሮናቫይረስ ይልቅ በትራፊክ አደጋ የሚጠፋው ሕይወት እንደሚበልጥ ጠቁመዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ በትራፊክ አደጋ ግን ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት መቅጠፉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ስራዎች በማጠናከር የተመዘገቡ ውጤቶችን እንደመነሻ በመውሰድ ለላቀ ውጤት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩ ስራዎች የአደጋውን መቀነስ የሚያመላክቱ ቢሆንም አሁንም የበለጠ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
ከፌዴራልና ከክልሎች የትራንስፖርት ባለስልጣን ቢሮዎች ጋር በተሰሩ ስራዎች ውጤት መገኘቱንም ገልጸው አሁንም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረምና የረጅምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን በማስቀመጥ ‘የዜጎችን ሕይወት በመታደግ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል’ ብለዋል።
በሚኒስቴሩ የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮናስ በለጠ ምክር ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት አምስት የመንገድ ደህንነት ምሰሶዎችን መሰረት በማድረግ አቅዶ ወደስራ መግባቱን ገልፀዋል።
እነዚህም መሰረተ ልማት፣ ጤና፣ ትምህርትና ግንዛቤ፣ ሕግ ማስከበርና የቁጥጥር ስራዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የእነዚህ ስራዎች መጠናከር ጠቋሚ የሞት መጠንን መቀነስ እንደመሆኑ በስድስት ወራት 15 ነጥብ 84 በመቶ ሞት መቀነሱን ጠቅሰዋል።