ነሀሴ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተካሄባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ።
በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በታክስ ሥወራ፣ በግብር ማጭበርበር፣ ያለደረሰኝ ግብይት በመፈጸምና ሐሰተኛ ማስረጃ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ለዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ ሀገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመመርመር ተገቢው የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የአሜሪካን ዶላር ለማውጣት የነበረውን ሙከራ በማክሸፍ እና የምርመራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ተጠርጣሪዎች ማረሚያ ቤት ወርደው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አንስተዋል።
በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ አሻጥሮችን በመቆጣጠር ፖሊስ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ምርመራቸው ተጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውንም ተናግረዋል።
በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሻጥር ለመፈጸም ሁኔታውን እየቀያየረ የሚገኘውን የወንጀል ተግባር ለመቆጣጠር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን አደራ ወደጎን በመተው በሌብነት ተግባር የተሰማሩ የመንግሥትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችንም ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ የተቋማት ኦዲት ሪፖርት ጉድለቶችን መነሻ በማድረግ የሕዝብና መንግሥት ሀብትን ላልተገባ ዓላማ ያዋሉ የሥራ ኃላፊዎችን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።