በመኖሪያ ቤት የተከማቸ 50 በርሜል ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) የአሶሳ ከተማ ፖሊስ በህገ-ወጥ መንገድ በግለሰቦች ቤት የተከማቸ 50 በርሜል ነዳጅ ከአራት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ በከተማው ለኑሮ ውድነት ምክንያት እየሆነ የመጣውን ህገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ለመቆጣጠር ፖሊስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ በግለሰቦች ቤት በተደረገ ፍተሻ 50 በርሜል ቤንዚን እና ናፍጣ ከአራት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በከተማው ቤንዚን እና ናፍጣ በጥቁር ገበያ በሊትር እስከ 200 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይቱ ምንጭ በህጋዊ መንገድ ከነዳጅ ማደያዎች ተቀድተው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ጥቂት ግለሰቦች እጅ መግባት እንደሆነ ፖሊስ እንደደረሰበት ኮማንደር ቡሽራ አስረድተዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የ90 ቀናት እቅድ በማውጣት ኅብረተሰቡን ከማወያየት ጀምሮ ህገ-ወጥ ነዳጅ ሽያጭን ለመቆጣጠርና ገበያ ለማረጋጋት ከተቋቋመው ግብረ-ኃይል ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል ፡፡
በቅርቡ በአሶሳ ከተማ በግለሰብ ቤት በበርሚል የተከማቸ ቤንዚን ባስነሳው የእሳት አደጋ በአንድ ሰው ላይ ጉዳት ሲያደርስ በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ካወደመ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ኮማንደር ቡሽራ አስታውሰዋል፡፡