በመዲናዋ ሀሰተኛ መታወቂያ ሲያትሙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) ሀሰተኛ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ የሚያባዙና የሚያሰሩ 7 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ፒያሳ “ሮቤል የጽሕፈት መሳሪያ መሸጫ” ተብሎ በሚጠራው ድርጅት ውስጥ ሀሰተኛ መታወቂያ እያተሙ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
ግለሰቦቹ አንድ ሀሰተኛ መታወቂያ ለማተም 10 ሺሕ ብር እየተቀበሉ እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ ወንጀል ሊፈጸምባቸው የሚችሉ እንደሆነም የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ከተጠርጣሪዎች ጋር በኤግዚቢትነት በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በኢትየጵያ ንግድ ባንክ አራዳ ጊዮርጊስ ቅርንጫፍ፣ በደቡብ ክልል ሀድያ ዞን ፍትሕና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ኤጀንሲ እና ሌሎች ተቋማት ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ ማህተሞች ተይዘዋል፡፡
ሀሰተኛ መታወቂያ ሲያባዙ የተያዙት ግለሰቦች በኅብረተሰቡ ጥቆማ የተያዙ ሲሆን አሁንም የመዲናዋ ነዋሪዎች ሀሰተኛ ሰነድ የሚሰሩ ሰዎችን መረጃ ለፖሊስ በመስጠት ወንጀለኞችን በማጋለጥ የሚያደርጉት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል፡፡