ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ 828 አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጠ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላገኙ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች በመሬታቸው ተጠቃሚ ለመሆን በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
አርሶአደሮች ይዞታውን በአግባቡ በማልማት እራሱን በመለወጥ ህይወቱን በዘላቂነት መምራት ይኖርበታል ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ለዓመታት ከተጠቃሚነት ርቀው የቆዩት የከተማዋና የአካባቢው አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው በተገቢው ሁኔታ እንዲካሱ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ አሠራሩን ፈትሾ ችግር የነበረበት መሆኑን በማረጋገጥ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የሁሉም መሰረቱ አርሶ አደሩ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር ለአርሶ አደሩ መሬቱ የሕይወት ዋስትናው በመሆኑ ተጠቃሚነቱን በማረጋገጥ ለከተማዋና ለሃገሪቱ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን አምባዬ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው ከተመዘገቡ 2 ሺህ 909 አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች መካከል በአጣሪ ኮሚቴ ተጣርቶ 1 ሺህ 200 በትክክለኛ ማስረጃ ተረጋግጦ ካርታ እንዲያገኙ መወሰኑንና ከእነርሱም መካከል ለ828 አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የካርታ መስጠት መርሐ ግብሩ የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ በቀጣይም አስፈላጊው ማጣራት እየተደረገ ሕጋዊ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሚያገኙ ማረጋገጣቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡