በመዲናዋ ለጌዴኦ የባህል ማዕከል የግንባታ ቦታ ተበረከተ

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ የጌዴኦ የባህል ማዕከልን ለመገንባት የሚያስችል የቦታ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ዓለሙ እና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አበባየሁ ታደሠን ጨምሮ የጌዴኦ ዞን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና እሴት ለማሳደግ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቁሟል።

እንደ ደራሮ ያሉ ያልተበረዙ የጌዴኦ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየትና የጌዲዮን ሕዝብና አካባቢ ባህላዊና ታሪካዊ ሃብት ለማስተዋወቅ እንዲሁም ለማልማት ማዕከሉ ትልቅ ሚና ይኖረዋል መባሉን የአሚኔ ዘገባ አመላክቷል።

ጌዴኦ የይርጋጨፌ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ሃብቶች መገኛ መሆኑ ይታወቃል።