በመዲናዋ ቄስ በመምሰል ሲንቀሳቀስ የነበረ ህወሓት ተላላኪ በቁጥጥር ስር ዋለ

መስከረም 11/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወረዳ 6 ገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ቄስ በመምሰል መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ግለሰቡ ራሱን የኦርቶዶክስ ቄስ በማስመሰል የአሸባሪ ቡድኑን እኩይ አላማ ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን በሰላም ሰራዊት አባላት ጥርጣሬ ክትትል መነሻ በፀጥታ ሃይሉ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በተደረገ ማጣራትም ምንም አይነት የቅስና ሙያ የሌለውና ራሱን ቀይሮ ለድብቅ አላማው ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑ መረጋገጡን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡ አሸባሪዎቹ የህወሓትና ሸኔ ቡድኖች የህዝባችንን ሰላም ለማወክ ምንጊዜም ያለእረፍት የሚሰሩ መሆኑን በመረዳት ከፊታችን ያሉ በዓላትም በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ፀጉረ ልውጦችን በትኩረት በመከታተል አካባቢውንና ከተማውን እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፏል!!