በመዲናዋ በህገወጥ መንገድ የተያዘ ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደረገ

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ በህገወጥ መንገድ የተያዘ ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት አመታዊ ሪፖርት በከተማዋ የተስተዋለው ህገወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል በልዩ ትኩረት ግብረ-ሃይል በማቋቋም በህገወጥ መንገድ የተያዘን መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለማቃለል ልዩ መመርያና የግምገማ ስርአት በመዘርጋት በመሬት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ 430 ሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔ በመወሰን ከቦታቸው እንዲነሱ መደረጉንም ነው ከንቲባዋ የጠቆሙት።

ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ የመጣውን የመሬት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠትም 40.34 ሄክታር መሬት ለመኖርያ ቤት ግንባታና 138 ሄክታር መሬት ሃገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች እና ለግል አልሚዎች በአስተዳደሩ ካቢኔ ወሳኔ መሰረት ማስረከብ መቻሉንም ነው የገለፁት።

የመኖርያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም በበጀት አመቱ በሶስት ፓኬጆች በላይ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ ምክትል ከንቲባዋ ማስታወቃቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬተሪ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመሰረቱ ለመፍታት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ተቋማት በጋራ ሽርክና በመፍጠር በቀጣዩ አምስት አመት አንድ ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ገልፀዋል።