የካቲት 24/2015 (ዋልታ) በመዲናዋ በተከሰተ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ንጋቱ ማሞ ለዋልታ እንደገለጹት ትላንት ከምሽቱ 12:36 ሰዓት ላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጉርድ ሾላ ንግድ ባንክ ጀርባ በደረሰ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
በእሳት አደጋው ሁለት መኖሪያ ቤቶችና 10 የንግድ ሱቆች መቃጠላቸውንና አንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛን ጨምሮ በሦስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 13 የእሳት አደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች፣ አንድ የውሀ ቦቴ፣ ሦስት አንቡላንስ እና 103 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መሰማራታቸውንም ጠቁመዋል።
የእሳት አደጋው ወደ አካባቢው ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ ባለበት ለመቆጣጠር የተቻለ ሲሆን የእሳት አደጋውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ እንደፈጀም አመላክተዋል፡፡
በእሳት አደጋው የወደመ ንብረት ግምት ለጊዜው አለመውጣቱ ነው የተገለጸው፡፡
በአድማሱ አራጋው