በመዲናዋ ከ297 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) ባለፉት 6 ወራ ለ227 ሺህ 500 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ297 ሺህ 696 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች ለከተማው ምክር ቤት የ6 ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት

የፀጥታ ሃይሉ ከሰላም ወዳዱ የከተማው ነዋሪ ጋር በመሆን ባደረገው የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ የጥፋት ሴራን መቆጣጠር እና የከተማውን ሰላም ማስጠበቅ ተችሏል፡፡

24 ሺህ የሚሆኑ የከተማው ወጣቶች የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል የበኩላቸውን ሚና የተወጡ ሲሆን “እኔ ለከተማዬ ሰላም ዘብ ነኝ’’ በሚል መሪ ቃል ለአካባቢያቸው ሰላም ዘብ በመቆም ለሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ተወጥተዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

400 የጤና ባለሙያዎች ወደተለያዩ የጦር ግንባሮች በማምራት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን ከመወጣት በተጨማሪ ባሸባሪው ትሕነግ ቡድን የወደሙ 18 የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም የተለያዩ የህክምና መድሃኒቶችንና መሳሪያዎችን በመላክ ከፍተኛ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ የዘማች አርሶ አደርና ሚሊሻ ቤተሰቦችን የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብ 30 ሺህ የሚሆኑ መምህራንና ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት በሰብል ስብሰባ በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፋቸውንና አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ከአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ግንባሮችን በመከፋፈልና የበሰለ ትኩስ ምግብና ቁሳቁሶችን ለሰራዊቱ በማቀበል ሰራዊቱን የማበረታታትና የማጀገን ሀላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ መደረጉን ተገልጿል፡፡

የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባራት እንደገና ለመወስን የከተማ አስተዳደሩ ባካሄደው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት መሠረት አዋጅ ቁጥር 74/2014 በዚሁ ምክርቤት ፀድቆ 71 የነበሩትን የመንግስት ተቋማት ወደ 46 በመቀነስ መልሶ የማደራጀት ስራ መሰራቱን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ለየት ያለ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያለው የህዝብ ድምጽ በአስፈፃሚው እንዲወከል በመስራት ከከተማ ካቢኔ ጀምሮ እስከታች ባሉ መንግስታዊ አደረጃጀት በቁጥር በከተማ ደረጃ 2 በክፍለ ከተማ ደረጃ 9 የሚደርሱ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በሃላፊነት እንዲመሩ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በአመራር ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 32% የደረሰ ሲሆን በምክር ቤቱም 49% ማድረስ መቻሉም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

አዲስ አበባን የሽብርና የሁከት ማዕከል በማድረግ ሀገርን ለማፍረስ የተያዙ እኩይ እቅዶችና ሙከራዎችን ሁሉ እንዲመክኑ ማድረግ ሲቻል ለአብነትም በፍተሻ፣ በብርበራና ተጥለው የተያዙ የቡድንና የነፍስ ወከፍ 850 የጦር መሣሪያዎችን ከ314 ሺህ 188 ጥይቶች ጋር እንዲሁም 88 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 84 መገናኛ ሬዲዮ፣ 2 የጦር ኮምፖስ እና 6 ጂፒኤስ መያዝ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ለሽብር ተግባር ሊውል የተዘጋጀን ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ የተለያዩ ሀገራት የውጪ ሀገር ገንዘቦች እና ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ብርም በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል፡፡

ለ1 ሺህ 514 ኢንተርፕራይዞች የካፒታል አቅማቸውን ለማሳደግ ከ449 ሚሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ታቅዶ 269 ሚሊዮን 247 ሺህ ብር መሰጠቱን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡