በመዲናዋ ከ7.4 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ

ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ በተያዘው በ2014 ክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል በ9 ችግኝ ጣቢያዎች ችግኝ የማፍላት የቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል፡፡

እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የችግኝ የጉድጓድ ቁፋሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ በሚቀጥለው ክረምት ከሚተከለው 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አራተኛው የአረጓዴ አሻራ ልማት ዘመቻ መርኃ ግብር ከሰኔ 18 እስከ 20/2014 ዓ.ም ድረስ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት እንደሚጀመርም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከተተከሉት 26 ሚሊዮን ችግኞች 80 በመቶ ችግኝ መጽደቁንም ምክትል ኃላፊዋ መናገራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW