በመዲናዋ የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች

አቶ አብርሃም ታደሰ

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ700 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ስራዎች መከናወናቸውን የከተማዋ የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ገለፀ።

የከተማዋ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ እንደገለጹት፤ የዘንድሮ ክረምት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በ14 ፕሮግራሞችና 19 መርሃ ግብሮች እየተከናወነ ነው፡፡

ሠብዓዊ አገልግሎት፣ ትምህርትና ስልጠና፣ አካባቢ ጥበቃና ውበት፣ ማዕድ ማጋራት፣ የትራፊክ አገልግሎትና የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎዎችን ጠቅሰዋል።

የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ስራዎችን ለመከወን መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

“በእስካሁን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ስራዎች ተከናውነዋል” ብለዋል፡፡

በክረምቱ ሶስት ሚሊየን ወጣቶች በተሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከ4 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው” በሚል እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ቤተሰብ ይዞ የሚደግፍበት አካሄድ መፈጠሩንም ገልፀዋል፡፡

በዚህም ለ20 ሺህ ቤተሰብ እማወራ እና አባወራ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ ለ18 ሺህ 202 ነዋሪዎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡