በመዲናዋ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ በዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት መቅረቡ ተገለጸ

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር በጣሊያን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ስነ ምግብ ኮንፈረንስ ላይ በተሞክሮነት መቅረቡ ተገልጿል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ የስነ ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የመንግስት አጀንዳ ሆኖ እየተሰራ እንደሚገኝ በዚህ ወቅት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የስነ ምግብ ዘርፍ አማካሪ ሜቲ ታምራት በከተማው እየተከናወነ ያለውን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተሞክሮን ከአዲስ አበባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው በጀት ዓመት ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በመመደብ በከተማዋ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።

በዚህም ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የተማሪዎችን ወጤት በማሳደግ፣ የመድገምና የማቋረጥ ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

በምገባ ፕሮግራሙ ምግብ በማብሰል ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ ተደርጓል ማለታቸውን የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ አመላክቷል።

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በአምስት ክፍለ ከተሞች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በመለየት የምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ የመመገቢያ ማዕከላትን በማቋቋም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዘጋጅነት በጣሊያን ሮም ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የስነ ምግብ ስርዓት ኮንፈረንስ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተሳትፈዋል፡፡