በመዲናዋ የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ሥራ

ነሐሴ 29/2013 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ 108 የመገበያያ ቦታዎች እና ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርት መዘጋጀቱን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
ከንቲባዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስራ የጀመሩት መሸጫዎቹ በከተማዋ የሚስተዋለዉን የኑሮ ዉድነት በማረጋጋት በተለይም የግብርና ውጤት የሆኑ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እንዲሁም እንደ እንቁላል ያሉ የእንስሳት ተዋጽኦ አቅርቦትን ይበልጥ በማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም 56 የቁም እንሰሳት መገበያያ እንዲሁም 52 የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫዎችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስራ ጀምረዋል።
መሸጫ ማዕከላቱ ለሸማቹ ህብረተሰብ ምርት በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ማሳ ከማቅረባቸው በተጨማሪ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ይህን መሰሉ ጥረት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡