በመዲናዋ የ43 አቅመ ደካሞች ቤት በማደስ የክረምት በጎ ፈቃድ ተጀመረ

ሰኔ 18/2013 (ዋልታ) – “በጎ ፈቃደኝነት ለመደጋገፍና መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በቂርቆስና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የ43 አቅመ ደካሞች ቤት በማደስ የክረምት በጎ ፈቃድ ተጀምሯል፡፡

በተያዘው ዓመት የሀገር ውስጥ ጉዲፍቻን ለማበረታታት 100 ህጻናት ቤተሰብ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንድ ልጅ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ መለስ ዓለም አንድ ልጅ በማሳደግ ግባር ቀደም ሆነዋል፡፡

በአዲስ አበባ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሀ ግብር ሁለት ሚሊየን በጎ ፈቃደኞች እንደሚሳተፋ እንዲሁም አንድ ቢሊየን ብር ሀብት በማሰባሰብ ለመስራትም እቅድ መያዙ ተመላክቷል፡፡

የክረምት በጎ ፈቃደኝነት ተግባራት እስከ መስከረም 30/2014 ዓ.ም ድረስ አንድ ሚሊየን 150 ሺህ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ በ14 ፕሮግራሞች በ19 መርሀግብሮች የሚተገበር ነው ተብሏል።

የበጎ ፈቃድ ስራው በሰብዓዊ አገልገሎት፣ በማህበራዊ አገልግሎት፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት፣ በጤናና ቀይ መስቀል፣ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት እና በሌሎችም ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተነግሯል።

በ2012/13 በጀት አመት የክረምትና በጋ የበጎ ፈቃድ ተግባር 2 ነጥብ 2 በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 877 ሚሊየን ሀብት በማሰባሰብ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ መደረጉን የከተማው የወጣቶች የበጎ ፈቃደኛ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በደም ልገሳ 37 ሺህ 767 ዩኒት ደም ማሠባሠብ እንደተቻለም ነው የከተማ አስተዳደሩ ያሳወቀው።

በማስጀሚያ መርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ መለስ ዓለም እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

(በምንይሉ ደስይበለው)