በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ጥቅምት 7/2015 (ዋልታ) የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የእቅድ፣ ክትትልና ግምገማ የስራ ሂደት ኃላፊ ተመስገን ተሰማ በበጀት አመቱ ከሀገር ውስጥ ታክስ 266 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር፣ ከወጭ ንግድ የጉምሩክ ቀረጥ ደግሞ ከ183 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ ከ450 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውሰዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሀገር ውስጥና ከወጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ በዘረጋቸው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አሰራሮች ግብር ከፋዮች በቀላሉ ግብር መክፈል መቻላቸው ገቢው እንዲጨምር አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

በሐሰተኛ ግብይቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር መጠናከር ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የሚሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆሙት ኃላፊው በአጠቃላይ ከ50 ሺሕ በላይ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW