በመጪው ሰኞ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የፈቀደውን እንዲመርጥ ጥሪ ቀረበ

ሰኔ 09/2013 (ዋልታ) – በመጪው ሰኞ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ለፈቀደው ፓርቲ እንዲሰጥ በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ የድጋፍ ሰልፍ ትናንት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

አቶ አሻድሊ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ በስድስተኛው ጠቅላላ  ምርጫ በክልሉ ካርድ የወሰዱ ዜጎች ሁሉ በነቂስ ወጥተው ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ መምረጥ አለባቸው፡፡

“ብልጽግናን ቢመርጡ ደግሞ ያስጀመርናቸውን በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶች አጠናክረን ከፍጻሜ እንደምናደርስ ቃል እገባላችኋለሁ” ብለዋል፡፡

ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ  ፓርቲው የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አሻድሊ፣ ህብረተሰቡም የአካባቢው ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፣ ፓርቲው የሀገሪቱን የውስጥ እና የውጭ ተጽእኖ ተቋቁሞ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ በመደመር እሳቤ የሚያምነው ብልጽግና በሃገራዊ አንድነት አይደራደርም ብለዋል፡፡

ፓርቲው ሀገራዊ አንድትን እና የብሔር ማንነትን በማጣጣም ሃገረ መንግስት ለመገንባት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ እየተጋ የሚገኘውን ብልጽግናን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በምርጫው ዕለትም እያንዳንዱ ህብረተሰብ አንድ ችግኝ በመትከል ለአረንጓዴ አሻራ እቅድ ስኬት የድርሻውን እንዲያበረክት አቶ ኢስሃቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ ኡመር መሃመድ ብልጽግናን መደገፍ እና መምረጥ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ከፓርቲው ደጋፊዎች መካከል ወይዘሮ አሚናት አብዱልዋሃድ በሰጡት አስተያየት “ባሳለፍነው 27 ዓመታት መብትና ግዴታችን በአግባቡ እንዳንወጣ ተደርገናል” ብለዋል፡፡

ብልጽግና አንድነትን በህብረብሄራዊነት በማጠናከር በሃሳብ የበላይነት ሀገር መገንባት የሚያስችል ፓርቲ በመሆኑ እንደሚደግፉት ገልጸዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጉደታ ነጋሳ ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን ካጠናከርን የሃገራችን የቀደመ ሠላም በቅርቡ ይመለሳል ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ራዕይ ሀገርን የሚጠቅም ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በድጋፍ ሰልፉ በአሶሳ ከተማ እና አካባቢው የሚኖሩ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡