በሚኒስትሯ የተመራ ልዑክ በዓለም የሥራ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) በሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጄኔቭ የተባበሩት መንግሥታት ዋና መሥሪያ ቤት በመካሄድ ላይ ባለው 110ኛው የዓለም የሥራ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

በጉባኤው 187 የዓለም ዐቀፉ የሥራ ድርጅት አባል ሀገራት መንግሥታት እንዲሁም የሠራተኞች እና አሠሪዎች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ሚኒስትሯ ሀገራቸውን በመወከል በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጊዜ የተከሰቱ ልዩ ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ያስከተሉትን ተፅእኖ በጥበባዊ የቀውስ ጊዜ አመራርና አስተዳደር እንዲሁም በኢትዮጵያዊ የመተባበር፣ የመተጋገዝ እና በመከራ ጊዜ በአንድ የመቆም እሴት በመቋቋም መሻገር መቻላቸውን አንስተዋል።

ለዚህም መንግሥትን እና መላውን ሕዝብ ማመስገናቸውን ከሚኒስትሯ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፉን የሥራ ድርጅት በተቀላቀለችበት መቶኛ ዓመት ዋዜማ ላይ የተካሄደው ጉባዔው ሀገሪቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እመርታ ለማምጣት የጀመረችውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሂደት እና በዚህም እየተገኘ ያለውን አበረታች ውጤት ለዓለም ለማሳወቅ ሰፊ እድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡