በብርሃኑ አበራ
መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ያጸናሉ ያሏቸውን ሁለት በማር የተለወሱ ረቂቅ አዋጆችን ለሀገሪቷ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራን ትኩረታቸው ያደረጉት እነዚህ ረቂቅ አዋጆች HR 6600 እና S3199 በመባል ይታወቃሉ፡፡
መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲል የሀገሬ ሰው፡፡ እነዚህ ስማቸው ያማረ ሊያሳኩት ያለሙት ተግባር የረከሰ ረቂቅ አዋጆች ዓላማ ከእጅ አዙር አገዛዝ የተለዩ አይደለም፡፡
አዋጆቹ በአሸባሪው ሕወሓት አመራር ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ገንዘብ ድጋፍ በአሜሪካን ኮንግረስ አባላት አማካኝነት የተዘጋጁ ሆነው ሳለ ስለ ኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ የሚያትቱ መሆናቸው እጅ አልሰጥ ያለችው ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ለመጠምዘዝ የሚያሴሩ ረቂቅ መሆናቸውን በግልጽ መረዳት ይገባል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ የዓለም ኃያላን ሀገራት አሁን በደረሱበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ባለው የዓለም ሁለንተናዊ መስተጋብር ውስጥ ልዕለ ኃያል ሆነው የመዝለቅ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ፈቃደኛ ባልሆኑ ሀገራት ላይ ተገቢ ያልሆኑ ዕርምጃዎችን በተቀናጀ መልኩ ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡
አንዳንዴ ወታደራዊ ባህሪ ሲኖራቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ በሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታ ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ማዕቀቦችን ለመጣል መንገድ የሚጠርጉ አዋጆችን ያወጣሉ፡፡ የነዚህ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ዓላማም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ከጦር ጣልቃ ገብነት በመለስ ምዕራባዊያን ተፎካካሪያቸውን የሚያጠለሹት፣ የተረጋጉ ሀገራትን የሚያፈራርሱት አንድም በፕሮፓጋንዳ አቅማቸው ሌላም መሰል ረቂቅ አዋጆች የሚፈጥሩትን የህግ ማዕቀፍ በመጠቀም በሚጥሏቸው ማዕቀቦች ነው፡፡
እነዚህ በማር የተለወሱ ረቂቅ አዋጆች ስማቸው ቢያምርም ሊያሳኩ ያለሙት ዓላማ ግን ኢትዮጵያን የሚያደማ ሆኗል፡፡
ረቂቅ አዋጆቹ ኢትዮጵያዊያንን በግለሰብ ደረጃ የሚጎዱና እያንዳንዱን ዜጋ የገፈቱ ቀማሽ የሚያደርጉ ሲሆን የአገሪቱን ሉዓላዊነት በመዳፈር ጭምር የተከፋፈለች፣ የተዳከመችና በቀላሉ ለምዕራባዊያን እጅ የምትሰጥ ለማድረግ ያለሙ መሆናቸው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ ረቂቆቹ ተቀባይነት አግኝተው ከጸደቁ የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት ያላገናዘቡና ኢ- ፍትሐዊነት የተስተዋለባቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ጨምሮ በተለያዩ የተቃውሞ ማሰሚያዎች በኢትዮጵያዊያን በኩል ጠንካራ እንቅስቃሴን የሚጠይቁ ናቸው፡፡
ረቂቅ አዋጆቹ እንደ ዓለም ባንክ፣ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ፈንድ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ መልሶ መገንባት እና ልማት ባንክ እንዲሁም ሌሎች መሰል ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ብድር እንዳይሰጡ ማገዳቸው በኢኮኖሚው ዘርፍ ከባድ መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡
ለጋሽ አገራትና ተቋማት እርዳታ እንዳይሰጡ ማስገደዳቸው፣ በኢትዮጵያ በለጋሽ አገራትና ተቋማት የሚተገበሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዳይፈጽሙ፤ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም እንዲቋረጡ መደንገጋቸው ድንቄም የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለመፍጠር የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆች ያስብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጆቹ ከጸደቁ ከአሜሪካ በተጨማሪ ሌሎች ሀገራትና ተቋማት ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸው ደግሞ አዋጆቹ ለኢትዮጵያዊያን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይዘው እንደሚመጡ ማስተዋል ይገባል፡፡
አዋጆቹ ከጸደቁ አሜሪካና ወዳጆቿ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ወታደራዊ እርዳታ፣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ የቴክኒክ እገዛና ስልጠናን ሙሉ ለሙሉ እንደሚያቆሙ፤ የተፈረሙ ስምምነቶች እንዲቋረጡ የሚያስችሉ አንቀጾች በረቂቆቹ መስፈራቸው ኢትዮጵያን በወታደራዊ መስክ ዳዴ ለማስባል አሜሪካ ቆርጣ መነሳቷን በገሃድ ያሳል፡፡
ይህ ሥነ-ምህዳራዊ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ መርምረው እውነታውን የተረዱ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ረቂቅ አዋጆቹ የሚያስከትሉትን መዘዝ እና ሴራ በማጋለጥ እንዳይፀድቁ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡
የረቂቅ አዋጆቹ ስምና ምግባር አለመገናኘቱን በተመለከተ አንድ ታሪካዊ እውነታ ማንሳት ይቻላል፡፡ በአድዋ ጦርነት ወቅት ባሻ አውአሎም ጨምሮ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን አባቶች አሜሪካዊያኑ የምክር ቤት አባላት ዛሬ ለመተግበር ያሰቡትን ተግባር ቀድመው ተግብረውት ነበር፡፡
በወቅቱ ጣሊያን ከምሽጉ እንዲወጣ በማሰብ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች መላ ዘየዱ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሰንበት ሥራ አይሰሩም፡፡ በሰንበት ብታጠቋቸው ታሽንፋላችሁ ሲል ባሻ አውአሎም ለጣሊያኖቹ ሹክ አላቸው፡፡ የተዘጋጀው መላ በጣሊያን የጦር መኮንኖች የሚታመን ሆነ፡፡ በእለቱ ኢትዮጵያዊያን ተዘጋጅተው እንደሚጠብቋቸው ያላወቁት ጣሊያኖች ከምሽጋቸው ወጡ፤ ድልም ተመቱ፡፡
እኛ የዚህ ታሪካዊ ገድል ከዋኞች የነባሻ አውአሎም ልጆች ነን፡፡ አባቶቻችን ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት የተገለገሉበትን እውቀት ዛሬ ማወቅ ይሳናቸዋል ብለው ማሰባቸው ምዕራባዊያን ዛሬም ያልተገነዘቡ መሆናቸውን ማሳያ ነው፡፡
ይህን መሰል ቀድመን የሰለጠንበትን የማልበሻና የማስማሚያ እውቀት በመጠቀም ረቂቅ አዋጆቹ ለሀገሪቱ መረጋጋት፣ ሰላምና የሰከነ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ያመጣሉ በሚል ከንቱ ሀሳብ ኢትዮጵያዊያንን ለመሸወድ የሚደረገው ሙከራ ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች እንዲሉት አይነት ይሆናል፡፡
እናም ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው እነዚህ ረቂቅ አዋጆች እንዳይጸድቁ የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡